ለኘሮጀክት ስራ የተቀጠሩ ሠራተኞች ኘሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የስራ ውላቸውም ይቋረጣል?

በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 10(1) (ሠ) ስር እንደተመለከተው አልፎ አልፎ የሚሠራ ስራ ማለትም ስራው የአንድ አሠሪ ቋሚ ስራ ሆኖ እየተቋረጠ ስራው በሚኖርበት ጊዜ ብቻ የሚሰራን ስራ ለመስራት የሚደረገው የስራ ውል ለተወሰነ ጊዜ እንደሚደረግ ውል ይቆጠራል፡፡ 

ስለዚህ በአንድ ድርጅት ውስጥ በኘሮጀክት ስራ የሚሠራ ሠራተኛ ኘሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የስራ ውሉም ይቋረጣል፡፡ በዚያ ድርጅት ስር ሆኖ በሌላ ቦታ ተመሳሳይ ስራ መኖሩ የተባለውን የኘሮጀክት ስራ አላለቀም የሚያስብል አይሆንም፡፡ ድርጅቱም የግድ ከአንድ ኘሮጀክት ወደ ሌላው ኘሮጀክት ሠራተኞችን ይዞ እንዲዞር የሚያስገድደው የህግ ነጥብ አይኖርም፡፡ 

በጥቅምት 11 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም በሰበር ችሎት የተሰጠ ውሳኔም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ተጠሪዎች ባቀረቡት ክስ መሠረት ተጠሪዎች በአመልካች ድርጅት ውስጥ በአናፂነት ሞያ ሲያገለግሉ ቆይተው ድርጅቱ ሌላ ስራ እያለው ስራው አልቋል በማለት ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የስራ ውላችንን አቋርጦብናል ስለዚህ አስፈላጊውን ክፍያዎች እንዲከፈልልን በማለት አመልክተዋል፡፡ 

ፍ/ቤቱም የስራ ውል መቋረጡ በአግባቡ መሆን አለመሆኑን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መርምሮ ምንም እንኳ የአሠሪው ቋሚ ስራ ቢሆንም አልፎ አልፎ የአናፂነት ስራው ሲኖር የሚሠራ መሆኑን ተረድቻለሁ በማለት የስራ ውሉ የተጠናቅቀው በአግባቡ ነው ሲል ወስኗል፡፡ 

ይግባኝ የተባለለትም ከፍተኛ ፍ/ቤትም በቅጥር ውላቸው ላይ “ለምን ስራ እና እስከመቼ” የሚለውን የማያስረዳ ባለመሆኑ የስራ ውሉ የተቋረጠው በአዋጅ ቁ.377/96 አንቀጽ 10(1) መሠረት ነው ማለት አይቻልም በማለት በስር ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ በመሻር ተጠሪዎች 8 ወር ውዝፍ ደሞዝ እንዲከፍላቸውና ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ሲል ወስኗል፡፡ 

 

የሰበር ችሎትም መዝገቡን ከመረመረ በኋላ እንደተገነዘበው ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ለምን ስራ እንደተቀጠሩ በሚለው ነጥብ ቀድሞውንም ያልተከራከሩበት ሆኖ ሳለ ይህ ለምን ስራ እስከ እስከመቼ ይሰራሉ የሚለውን ነጥብ ማየቱ በዚህ ጉዳይ ላይ አግባብነት የለውም፡፡ፍ/ቤቱም የስራውን መጠናቀቅና መኖር በድጋሚ በማስረጃ ማጣራት እየተቻለ ይህ ሳይደረግ ስንብቱ ያለ አግባብ ነው ብሎ መወሠኑ ህጋዊ መሠረት ያለው ሆኖ አላገኘውም፡፡ በመሆኑም ችሎቱ የከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር ስንብቱ በአግባቡ ነው ብሎ ወስኗል፡፡ 

ከዚህም መረዳት እንደሚቻለው ማንኛውም ድርጅት የራሱ የሆነ የአሠራር ስርዓት ሊኖረው ስለሚችል ተቀጣሪዎቹን የግድ ከአንድ ኘሮጀክት ወደ ሌላው ኘሮጀክት ይዞ  ለመሄድ የሚያስገድደው ህግ አለመኖሩን ነው፡፡ ስለዚህም በአንድ የስራ ምድብ በኘሮጀክት ስራ የተቀጠሩ ሰራተኞች ኘሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የስሪ ውላቸውም አብሮ ይቋረጣል፡፡ 

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት  ያግኙን

ኢሜይል  ፡-[email protected] 

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡

Scroll to Top