በስራ ላይ ስለሚደርስ አደጋና አሰሪው ስላለበት የካሳ ሀላፊነት

አንድ ሰራተኛ ስራውን በማከናወን ላይ ሳለ አሠሪው በመደበው የመጓጓዣ አገልግሉት ሲጠቀም አደጋ የደረሰበት እንደሆነ አሠሪው የጉዳት ካሳ መክፈል እንዳለበት በህጉ ላይ ተደንግጓል፡፡ 

ነገር ግን ለዚህ አደጋ ሶስተኛ ወገኖች ያደረጉት አስተዋፅኦ መኖሩ ከተረጋገጠ አሠሪው ካሳን ላለመክፈል እንደመከላከያ ነጥብ ሊጠቀምበት እንደማይችል በጥር 28 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የተላለፈው የሰበር ውሳኔ ያሳያል፡፡ 

ጉዳዩ መሠረት ያደረገው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን ሲሆን የተጀመረውም አመልካች ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ነው፡፡ አመልካችም በክሳቸው እንደገለፁት የአመልካች ሕጋዊ ባለቤት እና የአንዲት ህፃን አናት የሆኑት ሟች በተጠሪ መ/ቤት በኘሮጀክት ስራ አስተባባሪነት በሠራተኛነት ተቀጥረውና ልዩልዩ ጥቅማጥቅም ከደመወዛቸው በተጨማሪ እየተከፈላቸው በማገልገል ላይ እያሉ ተጠሪ ለመስክ ስራ ልኳቸው በመመለስ ላይ እንዳሉ ተጠሪ ለመስክ ስራ በግልፅ የመደበው መኪና ተገልብጦ ሟች ወድያው ህይወታቸው ማለፋን ገልፀው የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

ተጠሪም በመልሱ ላይ እንደገለፀው ሟች ህይወታቸው ባለፈበት ጊዜ ወደ ስራው መስክ የሔዱት ከተጠሪ ጋር የስራ ውል ከሌላቸው ከአመልካች ጋር መሆኑን የመኪና መገልበጥ አደጋው የደረሰውም በተከሳሽ ድርጅት የተመደበ ሹፌር እያለ አመልካች መኪናውን ከሹፌሩ በመቀበል በማሽከርከራቸው በመሆኑ የተከሳሽ ድርጅት ለአደጋው ሃላፊ ሊባል እንደማይችል ገልፀው ተከራክረዋል፡፡ 

የስር ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሟችና በተጠሪ መሃከል የአሠሪና የሰራተኛ ግንኙነት መኖሩ ተረጋግጧል በማለት ሲወስን የጉዳት ካሳውን በተመለከተ ደግሞ አደጋው በደረሰ ጊዜ መኪናውን የሟች ባለቤት የሆኑት አንደኛ አመልካች ሲያሽከረክሩ ስለነበር በስራ ላይ የደረሰ አደጋ ነው ሊባል አይችልም በማለት ተከሳሽ ድርጅት የስንብት ክፍያ ብቻ ሊፍል እንደሚገባ በመግለፅ ወስኗል፡፡ ይግባኝ የተባለለት ፍ/ቤትም በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 337 መሠረት ይግባኙን ሰርዟል፡፡

 

የሰበር ችሎትም “አደጋው የደረሰው የሰበር አመልካች ያላግባብ መኪናውን ከሹፌሩ በመቀበል ሲያሽከረክሩ ነው ተብሎ ተጠሪ የጉዳት ካሳ የመክፈል ሃላፊነት የለበትም ተብሎ መወሰኑ አግባብ ነው”? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን አግባብነት አላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር መርምሮታል፡፡ 

እንደመረመረውም ሟች ህይወታቸው ያለፈው ተጠሪ ለመስክ ስራ የመደበውን መኪና ከተጠሪ ሹፌር አንደኛ አመልካች በመቀበል ሲያስረክብ መሆኑ በግራ ቀኙ አልተካደም፡፡ ነገር ግን አመልካች በወቅቱ ወደ መስክ የሄዱት ከተጠሪ ፍላጎት ውጪ ነው ከመባሉ በስተቀር የተጠሪ ሠራተኛ ስለመሆናቸውም አልተካደም፡፡ 

በመሠረቱ በስራ ምክንያት ለሚመጡ ጉዳቶች አሠሪው ሃላፊነት አለበት፡፡ በአዋጅ አንቀፅ የ6(1) ላይ “አሠሪው ጥፋት ባይኖርም—“ ተብሎ መመልከቱ የአሠሪው የሃላፊነት አይነት ጥፋት ሳይኖር ሃላፊነት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ድንጋጌ በአንቀፅ 92(1)(ሐ) ስር የተመለከተው ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሠረት አሠሪው በመደበው የመጓጓዣ አገልግሎት ሠራተኛው ሲጠቀም ጉዳት ከደረሰ አደጋው በስራ ለይ እንደደረሰ ተቆጥሮ ሃላፊነቱን ከአሠሪው ሊወስድ የሚገበ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ይኸው ድንጋጌ አሠሪው የመደበው የመጓጓዝ አገልግሎት አደጋው ከደረሰበት በአሠሪው ስር ባለው ሌላ ሠራተኛ ወይም 3ኛ ወገን ከሆነ አሠሪው በተጐጂው ሠራተኛ የጉዳት ካሳ ሃላፊነት የሌለው ስለመሆኑ አያሳይም፡፡ በመሆኑም አመልካች የተጠሪን መኪና በወቅቱ ሲያሽከረክሩ የነበሩ መሆኑ መረጋገጡ ተጠሪን ነፃ ሊያደርገው የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች   የወሰኑት ውሳኔዎች መሠረታዊ የሆኑትን የአሠሪና ሠራተኛ ድንጋጌወችን ያላገናዘበ ነው በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሮአቸዋል፡፡ 

ተጠሪ ሃላፊነት አለባቸው ከተባለ ደግሞ የጉዳት ካሳ መክፈል ያለበት ለየትኞቹ የተጐጂ ጥገኖች የሚለውም ነገር ጠርቶ መታወቅ አለበት፡፡ በአንቀፅ 1ዐ7(1)(ሐ) ስር እንደተመለከተውም ማንኛውም በስራ ላይ የሚመጣ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የሞተ እንደሆነ ለጥገኖች የጡረታ አበል ወይም ዳረጐት ወይም ካሳ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ 

ነገር ህግ ህጉ ጥገኝነት ምን ማለት እንደሆነ ትርጓሜ  ያልተሰጠበት ቢሆንም ፍ/ቤቱ በሰጠው ትርጉም መሠረት ጥገኞች የሚለው ቃል ከሟች ምግብ፣ የመጠለያ፣የልብስና ለጤናው አጠባበቅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የሚጠይቁትን ወገኖች  የሚመለከት ነው፡፡ ስለሆነም አመልካች እራሱን ማስተዳደር የሚችልና ችግረኛ መሆኑ በቅድሚያ ያልተረጋገጠበት ሁኔታ ላይ ያለ በመሆኑ ብቻ የጉዳት ሳ የሚያገኝበት ምክንያት አይኖርም፡፡ 

በመሆኑም ፍ/ቤቱ አንደኛ አመልካች የሟተ ባል ቢሆኑም በቂ የሆነ የመተዳደሪያ ሀብት ያላቸው መሆኑ ስለተረጋገጠ የጉዳት ካሳ የሚያገኙበት ምክንያት የለም በማለት ወስኗል፡፡ ነገር ግን እንደ ሁለተኛ አመልካች የተቀመጠቸው የሟች ልጅ በህጉ የሟች ጥገኛ መሆኗ ስለተረጋገጠ የጉዳት ካሳ ያስፈልጋታል፡፡ 

ከዚህም የሰበር ውሳኔ መገንዘብ እንደሚቻለው በአንድ ሠራተኛ ላይ ጉዳት የደረሰው ሠራተኛው ወደ ስራ ሲሄድና ከስራ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሠሪው በመደበው የመጓጓዝ አገልግሎት ሲጠቀም መሆኑ ከተረጋገጠ 3ኛ ወገኖች ለአደጋው ያደረጉት አስተዋፅኦ ለአሠሪው መከላከያ መሆን እንደማይችል ነው፡፡ 

በተጨማሪም በአዋጅ 377/96 አንቀፅ 1ዐ7(1)(ሐ) ስር የተመለከተው “ጥገኞች” የሚለው ቃል መተርጐም ያለበት ከሟች የምግብ፣የመጠለያ፣የልብስና፣ለጤናው አጠባበቅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያሟላላቸው የሚጠይቁትን ወገኖች እንጂ ችግረኛ መሆኑ ያልተረጋገጠበት ወገን የሟች ሠራተኛ፣ባል፣ወይም ሚስት መሆኑ ብቻ ጥገኛ ሊያስብለው እንደማይችል ነው፡፡ 

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት ያግኙን 

ኢሜይል  ፡-[email protected]

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡

Scroll to Top