በባህላዊ ሆነ ሀይማኖታዊ ስርዓት የተፈጸመ ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት እስከሚመዘገብበት ጊዜ ድረስ የሚኖረው ህጋዊ ውጤት ምንድን ነው?

ሕጉ በሚፈቅደው የጋብቻ አፈፃፀም ስርአት መሠረት የተፈፀመ ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት እስከሚመዘገብበት ጊዜ ድረስ ላሉት ጊዜያቶች ህጋዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል ወይ? በዚህ ጊዜያት ውስጥ በህጉ ላይ የባልና ሚስት መብትና ግዴታ ተብለው የተገለፁት በእነዚህ ተጋቢዎች ላይ ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል ወይስ አይችልም?

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 28(1) ላይ ጋብቻው የተፈፀመው በማንኛውም የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ቢሆንም አግባብ ባለው የክብር ሹም መመዝገብ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

አንድ ጋብቻ ሕጉ በሚፈቅደው የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት በሆነው በአንዱ መንገድ ተፈፅሞ ነገር ግን ከላይ በተገለፀው ድንጋጌ መሰረት በክብር ሹም ሳይመዘገብ ቆይቶ ከዓመታት (ከጊዜያት) በኋላ ቢመዘገብ እስከሚመዘገብበት ጊዜ ድረስ ባሉት ጊዜያት በሕጉ ላይ የተደነገጉት የባልና ሚስት መብትና ግዴታዎች በእነዚህ ተጋቢዎች ላይ ተፈፃሚ ሊሆን ወይም ሕጋዊ ውጤት ሊኖረው አይችልም ማለት ነው?

ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁ.41896 በ26/06/2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት አመልካች ወ/ሮ ታደለች ዋለልኝ ተጠሪዎች ደግሞ እነ ወ/ሮ አዲስ አለም ፀጋው ተከራካሪ ወገኖች በሆኑበት መዝገብ ላይ ማብራሪያ ሰጥቶበታል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በአሁን አንደኛና እና ሁለተኛ ተጠሪዎች መካከል የነበረውን የጋብቻ ክርክር ተመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከ ቀበሌ 01/05 ክልል የሚገኘው የቤት ቁ.242 የሆነው ቤት የሁለቱ የጋራ ሐብት ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ደግሞ ይህ ውሳኔ መብቴን የሚነካ ስለሆነ ሊሰረዝ ይገባል በማለት በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.41358 መሠረት መቃወሚያ አቅርበው መዝገቡ ከተከፈተ በኋላ የአሁን አመልካችም በበኩላቸው በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41 መሰረት መቃወሚያ አቅርበው ከሁለተኛ የመቃወም ተጠሪ/ከአሁኑ ሦስተኛ ተጠሪ/ ጋር በትዳር እያለን በጋራ ያፈራነው መኖሪያ ቤት የመቃወም ተጠሪዎች ነው ተብሎ መወሰኑ መብቴን ስለነካ ሊሰረዝ ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

ጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበለት የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮ ጣልቃ ገብ (የአሁን አመልካች) ከ 2ኛ የመቃወም ተጠሪ (ከአሁን ሦስተኛ ተጠሪ) ጋር ጋብቻ የፈፀሙት በ 26/03/2000 ዓ.ም እንደሆነ በማስረጃነት የጋብቻ የምስክር ወረቀት የሚገልፅ ስላቀረቡና ይህ ክርክር ምክንያት የሆነው ቤት የመቃወም ተጠሪዎች የጋራ ሃብት ነው ተብሎ የተወሰነው በ 29/10/99 ዓ.ም ስለሆነ ንብረቱ የጣልቃ ገብ (የአሁን አመልካች) እና የ 2ኛ የመቃወም ተጠሪ (የአሁን 3ኛ ተጠሪ) የጋራ ሐብት የሚሆንበት የሕግ አግባብ የለም በማለት አቤቱታውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ምንም እንኳ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌ/ከፍ/ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ፍ/ቤቱ የስር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ጉድለት የሌለው ነው በማለት ይግባኝ ማመልከቻቸውን ሰርዞባቸዋል፡፡

የሰበር ችሎቱ ይህንን ጉዳይ ሊያይ የቻለው አመልካች በበታች ፍ/ቤቶች ከላይ በተገለፀው መልኩ በሰጡት ውሳኔ ቅር በመሰኘታቸው ምክንያት አቤቱታቸው ለሰበር ችሎት በማቅረባቸው ነው፡፡

ሰበር ችሎቱም አቤቱታውን ከመረመረ በኋላ አመልካች ከሦስተኛ ተጠሪ ጋር በባህል የተጋባነው በ1992 ዓ.ም ነው እያሉ የስር ፍ/ቤት ክርክር የተነሳበት ንብረት ከመጋባታቸው በፊት ነው በማለት የአመልካችን አቤቱታ ሳይቀበል መቅረቱ ሊመረመር ይገባል በማለት ተጠሪዎችን እንዲቀርቡ ቢያዙም 1ኛ አና 2ኛ ተጠሪ መጥሪያ ደርሷቸው ሲቀርቡ እንደዚሁም 3ኛ ተጠሪ ከአመልካች ጋር በባሕል የተጋቡት በ1992 ዓ.ም እንደሆነ ገልጾ በአቤቱታው መሰረት ቢወሰን ተቃውሞ የለኝም የሚል መልስ ያቀረበ መሆኑን ችሎቱ በመግለፅ ጉዳዩን እንደሚከተለው በመመርመር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አመልካች ከሦስተኛ ተጠሪ ጋር በ1992 ዓ.ም በባሕል መጋባታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ በአስረጂነት ለስር ፍ/ቤት ማቅረባቸውን ተገንዝበናል የስር ፍ/ቤቶች ለውሳኔያቸው መሰረት በማድረግ የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ ሊያደርጉ የቻሉት ከላይ የተገለፀው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 28(1) በመጠቀም አመልካች ሦስተኛ ተጠሪ የፈፀሙት ጋብቻ በ 26/03/2000 ዓ.ም በክብረ መዝገብ ሹም መመዝገብ አለበት የሚለውን በመመልከት ነው፡፡

ሆኖም ምንም እንኳ በዚህ ንዑስ አንቀጽ 28(1) ላይ ጋብቻው የተፈፀመው በማንኛውም የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ቢሆንም አግባብ ባለው የክብር ሹም መዝገብ እንዳለበት የተገለጸ ቢሆንም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) ላይ የጋብቻው ሕጋዊ ውጤት የሚኖረው ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን ጋብቻው ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የተመላከተ በመሆኑ የበታች ፍ/ቤቶች ከአመልካች ለቀረበላቸው ጥያቄ አመልካች እና ሦስተኛ ተጠሪ ጋብቻ የፈፀሙበትን ጊዜ በማረጋገጥ  ከዚህ ቀን ጀምሮ ጋብቻው ህጋዊ ውጤት ያለው መሆኑን መወሰን ሲገባቸው ጋብቻው በክብር ሹም የተመዘገበበትን ቀን መሠረት በማድረግ ከዚህ በፊት ጋብቻ ስለሌለ አቤቱታው ተቀባይነት የለውም በማለት የሰጡትን ውሳኔ ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጐታል፡፡

ከዚህ ልንረዳው የምንችለው ነገር አንድ ጋብቻ ምንም እንኳ ህጉ በክብር ሹም ፊት መመዝገብ እንዳለበት ቢደነገግም የጋብቻው ሕጋዊ ውጤት የሚጀምረው ጋብቻው ህጉ በሚፈቅደው ስርዓት ከተፈፀመበት ቀን እንጂ ጋብቻው ከተመዘገበበት ቀን አለመሆኑን ነው፡፡

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል ፡-[email protected]

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ  የውርስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፍቺ ጠበቃ፣ … ማግኘት ይችላሉ፡፡

Scroll to Top