አንድ ሠራተኛ ወደ ስራው እንዲመለስ ሊወሰን የሚችለው መቼ ነው ?

የአንድ ሠራተኛ የስራ ቅጥር አለአግባብ ከተቋረጠ ፍርድ ቤተ ወደ ስራው እንዲመለስ ወይም ካሳ ተከፍሎት መሰናበት እንዲችል እንዴት መወሰን እንዳለበት በአዋጅ ቁ.377/96 አንቀፅ 43 ንዑስ አንቀጽ 2 ተንግጓል፡፡ 

በዚህም መሠረት ፍ/ቤቱ አንድ ሠራተኛ ወደ ስራው እንዲመለስ የሚወሰነው ከስራ ግንኙነቱ ጠባይ የተነሳ የስራ ግንኙነቱ ቢቀጥል ከፍተኛ ችግር ሊከተል ይችላል ብሎ በማያምንበት ጊዜ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በጥበቃ ስራ የተሰማራ ሰውም የስራው ውል ያለአግባብ በሚቋረጥበት ግዜ በአሠሪውና ሰራተኛው መሃከል የሚጠይቀው ከፍተኛ የሆነ መተማመን ስለሚሻክር ፍ/ቤቶች ካሳን እንዲከፍለው በማድረግ ከስራ እንዲሰናበት ማድረግ እንደሚገባቸው በታህሳስ 16 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የተላለፈው የሰበር ውሳኔ ያስረግጣል፡፡ 

ጉዳዩ የታየው በፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ሰራተኛ ተቀጥሮ በማገልገል ላይ እያለ የስራ ውሉ ያለአግባብ ተቋርጧል በማለት ከወሰነ በኋላ የተጠሪን ወደስራ የመመለስ ጥያቄ ውድቅ ማድረግ ልዩ ልዩ ክፍያዎች ተከፍሏቸው ወደስራ እንዲመለሱ ወስኗል፡፡ 

በውሳኔው ቅር በመሰኘት ሁለቱም ወገኖች ይግባኝ ቢያቀርቡም ከፍተኛው ፍ/ቤት የአመልካችን ይግባኝ በመሠረቱ ተጠሪን ደግሞ ወደስራ አይመለሱ ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ አግባብ አይደለም በማለት የ8 ወር ደሞዝ ተከፍሎአቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ በማለት ወስኗል፡፡ 

የሰበር ሰሚ ችሎትም ጉዳዩን እንደመረመረው የመጀመሪያው ደረጃ ፍ/ቤት ተጠሪው ወደ ስራው መመለሱ በአሠሪውና ሰራተኛው ግንኙነት ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊና አዎንታዊ ጐን በመመዘን ተጠሪ የከሳሽ አስፈላጊ ክፍያዎች ተከፍለውት ከስራው እንዲሰናበት ወስኗል፡፡ በዚህ መሰረት ከህጉ አንፃር ሲታይ የተጠሪ የስራ ባህሪይ የአመልካች ድርጅት ጠቅላላ ንብረት ፀጥታና ደህንነት መጠበቅ ከመሆኑ አንፃር የስራ ግንኙነቱ ቢቀጥል በአመልካች ድርጅት ከፍተኛ የሆነ ጉዳትና ችግር ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ከፍተኛው ፍ/ቤት ይህንን ወደ ጐን በመተው ተጠሪ ወደ ስራው እንዲመለስ በማለት የሰጠው ውሳኔ አግባብ ባለመሆኑ ሽሮታል፡፡ 

 

ስለዚህም በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማራ ሰው የስራው ውል ያለአግባብ እንደተቋረጠ በፍ/ቤት ውሳኔ ከተሰጠ ፍ/ቤቶቹ የካሳ ክፍያ እንዲከፍል ማድረግ እንጂ ሠራተኛው ወደስራ ቦታው እንዲመለስ ማድረጋቸው ተገቢ እንዳልሆነ፣ አንድ ሠራተኛ ወደ ስራው እንዲመለስ የሚወሰነው ከስራ ግንኙነቱ ጠባይ የተነሳ የስራ ግንኙነቱ ቢቀጥል ከፍተኛ ችግር ሊከተል ይችላል ተብሎ በማይታመንበት ግዜ ብቻ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ 

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት ያግኙን 

ኢሜይል [email protected]

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡

Scroll to Top