የፍ/ብሔር ግንኙነት በሚቋቋምበት ጊዜ ይህ ግንኙነት ክርክር ቢያስነሳ ተከራካሪዎች የሚለያዩባቸውን ነጥቦችን ለማስረዳት መቅረብ ያለበት ማስረጃ በህጉ የተወሰነ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የፍ/ብሔር ግንኙነቶች ክርክር ሲያስነሱ በምስክር ወይም በተለየ ማስረጃ መረጋገጥ ያለባቸው መሆኑ በህግ ተለይተው ተመልክተዋል፡፡
የገንዘብ አደራን በተመለከተ ሊቀርብ የሚገባውን የማስረጃ አይነት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2472 ላይ የተቀመጠ ሲሆን በዚህም መሠረት ለአደራ ተቀባዩ የተሰጠው እቃ ጥሬ ገንዘብ የሆነ እንደሆነ አደራ ተቀባዩ እንዲገለገልበት ተፈቅዶለት ከሆነ እንደዚህ ያለው ጉዳይ የአለቀ ነገርን ብድር የሚመለከቱ ደንቦች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ይገልፃል፡፡
በመሆኑም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2472(1) መሠረት ከብር 500.00 ብር በላይ ሲሆን የብድሩ ውል በፅሑፍ ወይም በፍርድ ቤት በተደረገ የእምነት ቃል ወይም መሀላ ካልሆነ በቀር ማስረዳት እንደማይቻል ተገልጿል፡፡
ይህንን በተመለከተ በሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ በአመልካች አቶ ታደሰ ደምሬ እና በተጠሪ አቶ ጌታሁን ለቻሞ መካከል ሲሆን ተጠሪ ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ለአመልካች ብር 180,000.00 ለጊዜው በአደራ አስቀማጭነት ከሰጡ በኋላ ገንዘቡን ለመመለስ አመልካች ሲጠየቁ ሊመልሱ ያልቻሉ መሆኑን ጠቅሰው ገንዘቡን ከእነወለዱ እንዲመልሱላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
አመልካች ከሰጡት መልስም ተጠሪ ለክሱ መሠረት የሆነውን ገንዘብ በአደራ ያልሰጧቸው መሆኑን ገልፀውና ለጉዳዩ ማስረጃዎች በተጠሪ በኩል ያልቀረቡባቸው መሆኑን ገልፀው ቢከራከሩም ጉዳዩን ያየው ፍ/ቤት አመልካቹን ለክሱ ሀላፊ በማድረግ ለክሱ መሠረት የሆነውን ገንዘብ ከነሕጋዊ ወለዱ ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡
ጉዳዩ በሰበር ችሎት የታየ ቢሆን በጉዳዩ የተጠሪ ክርክር ብር 180,000.00 ለአመልካች በጊዜው በአደራ ሰጥቼው ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የገንዘብ መጠን ከ 500.00 ብር የበለጠ በመሆኑ በህጉ አግባብ ተብሎ ሊያዝ የሚችለው ማስረጃ በፅሁፍ ወይም በፍ/ቤት በተደረገ የእምነት ቃል ወይም መሃላ ነው እንጂ ምስክሮችን ማቅረብ አይደለም በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሯል፡፡
በመሆኑም ከዚህ መረዳት የሚቻለው ማንኛውም በአደራ ገንዘብን ለማስቀመጥ የተደረገ ስምምነት ግዴታ በፅሁፍ ወይም ፍ/ቤት በተደረገ የእምነት ቃል ወይም መሃላ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ነው፡፡
ተጨማሪአስተያየትወይምጥያቄካለዎትያግኙን፡፡ ኢሜይል ፡- [email protected]
አግባብነትያላቸውተጨማሪየህግመረጃዎችከማናቸውምኢትዮጵያዊጠበቃ፣ኢትዮጵያዊታክስጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየቤተሰብጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየወንጀልጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየንብረት/ውርስጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየካሳጠበቃ፣ኢትዮጵያዊፍቺጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየጉዲፈቻ ጠበቃ … ማግኘትይችላሉ፡፡