የሀይማኖት ተቋማት ተቀጣሪዎች ጉዳይ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ሊታይ ይችላል?

በአዋጅ ቁጥር 42/85 አንቀፅ 3(3)(ለ) እንደተደነገገው የሀይማኖት ወይም የበጎ አድራገት ድርጅቶች በሚመሰርቱት የስራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ ተፈፃሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ሊወስን ይችላል በሚል ይደነግጋል፡፡ ታዲያ ይህ ማለት በአንቀጽ 3(3)(ለ) መሠረት የተጠቀሱት ድርጅቶች በሚመሰርቱት የስራ ግንኙነት አዋጅ ተፈፃሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እስካላወጣ ድረስ አዋጁ በነዚህ ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚነት አለው ማለት ነው?   

በፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት የተጀመረው ጉዳይ እንደሚያየው በሃይማኖት ተቋም ስር በዲያቆንነት ሲያገለግሉ የነበሩት ተጠሪዎች የስራ ውላችን ያለ አግባብ ስለተቋረጠ ወደ ስራ እንድንመልስ ይወሰንልን በማለት ክስን መስርተዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የአዋጅ ቁ.42/85 ተፈፃሚ በማድረግ ስንብቱ ህገ ወጥ ነውና ሠራተኞቹ ይመለሱ በማለት ሲወስን ከፍተኛ ፍ/ቤቱም ውሳኔውን አፅንቶታል፡፡ 

ጉዳዩ የሰበር ችሎት በይግባኝ በመቅረቡ ችሎቱ አዋጅ ቁ.42/85 አንቀፅ 3 ላይ የተመለከተውን ነጥብ የሕግ ትርጊም መሰጠት እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡ 

በመሰረቱ ሕጉ በአጠቃላይ ከአሠሪና ሰራተኛ ግንኙነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በአንዳንድ ሁኔታዎች ከሚያጋጥሙ ልዩ ጉዳዮች በቀር አካቶ የያዘ መሆኑን መረዳት ይቻላል በአንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ ሊመሰረት የሚችል የተለያየ የስራ ግንኙነት ሊኖር ይችላል ምክንያቱም በአንድ በኩል የሚሰጡት አገልግሎት ድርጅቱ ከሚተለው እምነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውና ከእምነቱ ጋር ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ሰራተኛ (ቄስ፣ዲያቆን ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሚሰጡት አገልግሎት ከእምነቱ ጋር ያልተቆራኘ እንደ የሒሳብ ሰራተኛ ያሉ አሉ፡፡ 

ቀጥተኛ ከሃይማኖት ወይም መንፈሳዊ ስራ የሚሰሩትን ሰራተኞች ስንመለከት የስራቸው ፀባይ የሃይማኖት ተቋሙ ከሚከተለው እምነት የሚመነጭና ከእምነቱ ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ የመንፈሳዊ ግንኙነቱ የሚያስነሳቸው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ከእምነቱ ተነጥለው የሚታዩ ባለመሆናቸው በስራ ግንኙነት ውስጥ ጣልቃ መግባቱ በእምነት ውስጥ ጣልቃ መግባትን ያስከትላል፡፡ 

 

የመንፈሳዊ የስራ ግንኙነቱ የሚያስነሳቸው ሁኔታዎች ከሃይማኖት ተነጣጥለው ሊታዩ አይችሉም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንፈሳዊ ግንኙነትን በተመለከተ የሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባት ይሆናል ይህ ደግሞ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 11 ላይ የተቀመጠውን “መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም” የሚለውን የሚፃረር ይሆናል፡፡ 

ስለዚህ በአዋጅ ቁጥር 42/85 አንቀጽ 3(3)(ለ) መሠረት ሊወጣ የሚችለው ደንብ ሊመለከቱት የሚቻለው የሚሰጡት አገልግሎት ከእምነቱ ጋር ላልተቆራኘ ሠራተኛ እንጂ የመንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነቶች የሚጨምር ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን በማለትም ችሎት የስር ፍ/ቤት ውሳኔዎችን ሽሮአቸዋል፡፡ 

ከዚህም መረዳት የሚቻለው ማንኛውም የስራ ክርክር ሰሚ አካላት መንፈሳዊ የስራ ግንኙነቶች ላይ ተመስርተው የሚነሱ ክርክሮች በአዋጅ ቁጥር 42/85 መሠረት ለመወሰን ስልጣን የሌላቸው መሆኑንና የሃይማኖት ተቋማቱ በሚኖራቸው አለመግባባቶችን ሚፈቱበት መንገድ የሚታዩ መሆን እንዳለባቸው ነው፡፡ 

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት ያግኙን 

ኢሜይል  ፡-[email protected]

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡

Scroll to Top