አንድ ባለጉዳይ በአቃቤ ህግ በኩል የአሠሪና ሠራተኛን ግንኙነት በተመለከተ የተመሠረተ የወንጀል ክስ ላይ ነፃ በመውጣቱ ብቻ ወደ ቀድሞው ስራዬ ልመለስ ሌሎች ክፍያዎችም ሊከፍሉኝ ይገባል ማለት አይችልም፡፡ 

ይህ የሆነበት ምክንያትም በመሰረቱ የወንጀል ክስና የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅን መሠረት አድርጎ የሚቀርብ ክስ የተለያየ ይዘትና አላማ ያላቸው ከመሆኑም በላይ በማስረጃ አመዛዘን ረገድም የተለያዩ መርሆችን መሠረት የሚያደርጉ መሆናቸው ነው፡፡

በህዳር ዐ4 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የሰበር ችሎትም የሰጠው ውሳኔ ይህንን የሚያስረግጥ ነው፡፡ ጉዳዩ በአመልካች በአዲስ አበባ የምግብ አዳራሽ አስተዳደር እና በተጠሪ ወ/ሮ የውብዳር ጥላሁን መሃከል ሲሆን ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ውስጥ እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ በአቃቢ ሕግ በኩል ክስ በመመስረቱ የስራ ውላቸው ተቋርጦ መቆየቱና በኋላም ይኸው ክስ በመዘጋቱ ምክንያት ወደ ስራ የመለሳቸው ቢሆንም የተቋረጠውን ደሞዝ ያልከፈላቸው መሆኑንና ወደ ቀድሞም ስራ ያልመለሷቸው ስለሆነ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን አይቶ ውሳኔ ይሰጥላቸው ዘንድ ክስ መስርተዋል፡፡ 

አመልካችም በፍ/ቤቱ ጥሪ መሰረት ቀርቦ ተጠሪ ከስራ የታገዱበት ገንዘብ አጉድለው በመገኘታቸውና የተወሰነ ገንዘብ መልሰው ቀሪውን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸውን ወደ ቀድሞው የስራ መደብ ለመመለስ ያልቻለው ከተጠሪ ጥፋት አንፃር መሆኑንና ባልነበሩበት ጊዜ የደሞዝና የጥቅማጥቅም ጥያቄ ማቅረብ የማይችሉ መሆናቸውን በነጥብነት በማንሳት ተከራክሯል፡፡ 

ጉዳዩን የተመለከተው ፍ/ቤትም ጉዳዩን መርምሮ የስራ ውል የሚሻሻልበትን የሕግ ምክንያት በመዘርዘርና አመልካች የስሪ መደቡን ስቀይር የስራ ውል የማሻሻል ውጤት የሚኖረው መሆኑን በመግለፅ የአመልካችን እርምጃ ሕገ ወጥ በማለት ወስኗል፡፡ ጉዳዩን በይግባኝ ያየው ፍ/ቤትም ይግባኙን ሰርዟል፡፡ 

የሰበር ችሎቱም በቀረበለት ማመልከቻ እንደተገነዘበው ተጠሪ በገንዘብ ያዥነት የስራ መደብ ተቀጥረው ሲሠሩ መቆየታቸው በስራው አጋጣሚ ወደ እጃቸው ከገባው ከአመልካች ገንዘብ ውስጥም 4219.00/አራት ሺህ ሁለት መቶ ብር/ አጉድለው ብር 950.00/ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ብር/ መልሰው ቀሪውን ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከስራ ታግደው መቆየታቸውንና የዓቃቤ ህግ በኩል ክስ መመስረቱ የተረጋገጡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ተጠሪ በተመሠረተው በወንጀል ክስ ነፃ ስለወጣሁ ወደ ቀድሞ ስራ ልመለስ ይገባል ብለዋል፡፡ 

ነገር ግን የወንጀል ክስና የማስረጃ ምዘናው ከምክንያታዊ ጥርጣሬ የፀዳ ሲሆን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን መሠረት የሚያደርግ ክስ በባሕሪው ከዲስፒሊን እርምጃ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የማስረጃ ምዘናው ለየትያለ ነው፡፡ በመሆኑም በወንጀል ተከሶ ነፃ የሚወጣ ሠራተኛ በዲስኘሊን ቢከሰስ አጥፊ ሆኖ የመገኘት ዕድሉ ሰፊ ሊሆን ይችላል፡፡ 

ይህ ጉዳይ ሲታይም አመልካች ተጠሪን ወደቀድሞው ስራ ባይመልሳቸውም በሌላ የስራ መደብ እንዲሰሩ ፈቅዷል፡፡ የስር ፍ/ቤቶቹም ይህንን እርምጃ ህገ ወጥ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሱት በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 25 ስር የተዘረዘረውን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን አመልካች የተጠሪ የስራ መደብ ለውጥ ያደረገው ተጠሪ የገንዘብ ጉድለት ስለአስከተሉ በመሆኑ ህገወጥ ነው ሊባል የሚገባው አይደለም፡፡ አግባብነት ያለውን የስራ መደብ መስጠት የሚሰራው ሃላፊነትም ከአሰሪው የአስተዳደር ስራ ነፃነት ጋር ተያያዥነት ያለው ነው፡፡ 

በአጠቃላይ የስር ፍ/ቤቶች የአመልካች እርምጃ ህገወጥ ወደሚለው ድምዳሜ የደረሱት የህጉን አጠቃላይ መንፈስ መሠረት ያላደረገ በመሆኑ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት የስር ፍ/ቤት ውሳኔዎችን ሽሯል፡፡ 

ተጨማሪ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት  ያግኙን

ኢሜይል  ፡-[email protected]

አግባብነት ያላቸው ተጨማሪ ህግ መረጃዎች ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ ታክስ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የወንጀል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንብረት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የካሳ ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የንግድ ምልክት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኢሚግሬሽን ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የፓተንት ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊ የኮፒራይት ጠበቃ… ማግኘት ይችላሉ፡፡