ፍቺ ምክኒያቱና ውጤቱ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ቤተሰብ ህግ መሰረት

ስለ ፍቺና ዉጤቶቹ ማወቅ ይፈልጋሉ ? እንግዲያው የኢትዮጵያ ቤተሰብ ህግ ስለፍቺ፣ ምክኒያቱና ውጤቱ የደነገገውን ከዚህ እንደሚከተለው አስቀምጠንልዎታል፡፡ በኢትዮጵያ ህግ መሠረት ጋብቻ እንዴት መፍረስ  እንደሚችል በኢትዮጵያ የተሻሻለው ቤተሰብ ህግ ውስጥ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በኢትዮጵያ ሦስት አይነት የጋብቻ አይነቶች አሉ፡፡ እነርሱም ሀይማኖታዊ ጋብቻ፣ ባህላዊ ጋብቻ፣ ህጋዊ/ሲቪል ጋብቻ ናቸው፡፡ የጋብቻው አይነት ይለያይ እንጂ የሁሉም አይነት ጋብቻ መፍረሻው ሁኔታና ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡

 ጋብቻ ሊፈርስ  የሚችልባቸው ሦስት ምክንያቶች

1ኛ. ከተጋቢዎቹ አንደኛው የሞተ እንደሆነ ወይም መጥፋቱ በፍርድ ቤት የታወጀ ከሆነ፣

2ኛ. ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ካላባቸው መስፍርቶች መካከል አንዱ ሳይሟላ ቀርቶ በፍርድ  ቤት እንዲፈርስ ሲደረግ እና፣

3ኛ. በፍቺ 

ጋብቻ እንዴት በፍቺ ሊፈርስ ይችላል

ጋብቻ በሁለት መንገዶች በፍቺ ሊፈርስ ይችላል፡፡

1ኛ. ባልና ሚስቱ በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ስለፋቺያቸውና ውጤቱም ዝርዝር ስምምነት አድርገው ይህንኑ ለፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ፣ወይም

2ኛ. ሁለተኛው ደግሞ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍ/ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው፡፡ 

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ቢኖር ተጋቢዎች ፈትቼሻለሁ፣ ፈትቼሀለው፣  ተፋተናል በመባባል ተለያይተው በተለያያ ቦታና ሀገር መኖራቸው እንኳ ጋብቻን አያፈርሰውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጽሁፍ ስምምነት ሆነ በቤተዘመድ ጉባዔ ፍቺን ማድረግ አይቻልም፡፡ የህግ ውጤትም የለውም፡፡ ስለሆነም አንድ ፍቺ ፍቺ ሊባል የሚችለውም ሆነ የህግ ውጤት ሊኖረው የሚችለው ፍቺው በፍርድ ቤት ጸድቆ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ 

 

ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር ማንኛውም ፍቺን የሚጠይቅ ወገን ለመፍታት የወሰነበትን ምክኒያት እንዲገልጽ ግዴታ የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ 

አንደኛው የፍቺ መንገድ/ የስምምነት ፍቺ

ከመጀመሪያው ብንነሳ የስምምነት ፍቺ የሚደረገው ባልና ሚስቱ በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ስምምነታቸውንና ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤት በጽሁፍ ለፍርድ ቤት  እንዲፀድቅላቸው ሲያቀርቡትና ፍርድ ቤቱም ሲያጸድቀው ነው፡፡ ሆኖም ግን ተጋብተው ገና ስድስት ወር ያልሞላቸው ተጋቢዎች በስምምነት መፋታት አይፈቀድላቸውም፡፡ በፍቺ ስምምነታቸው ላይ ለመፍታት የወሰኑበትን ምክንያት እንዲገልፁ አይገደዱም፡፡ 

በዚህ ጊዜ ፍ/ቤት ባልና ሚስቱን ለየብቻ ወይም በአንድ ላይ በማስቀረብ ስለጥያቄያቸው ያነጋግራቸዋል፡፡ በዛውም የመፋታት ሀሳባቸው እንዲለውጡ ተገቢውን ጥረት ያደርጋል፡፡ ሀሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ እንደሁኔታው ከሦስት ወር ያልበለጠ የማሰላሰያ ጊዜ በመስጠት ሊያሰናብቻቸው ይችላል፡፡ ሀሳባቸው በመፋታት ያፀኑ ከሆነ የማሰላሰያው ጊዜ ካበቃበት ቀን አንስቶ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን እንደገና አንቀሳቅሰው የፍቺ ስምምነታቸውን እንዲያፀድቅላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ይህ ገደብ ግን ባልና ሚስቱን አዲስ የፍቺ ስምምነት እንዲያቀርቡ አያግዳቸውም፡፡ 

የባልና ሚስቱ የፍቺ ፍላጐት ትክክለኛና ፈቃዳቸውን በነፃ የሰጡ መሆኑ ተረጋግጦ ስምምነቱ ከህግና ከሞራል ጋር ካልተቃረነ ፍ/ቤቱ የፍቺ ስምምነቱን ያፀድቀዋል፡፡ ፍቺውን ሲያፀድቅ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ያደረጉትን ስምምነትም አብሮ ያፀድቃል፡፡ ባልና ሚስቱ ስለፍቺው ውጤት ያደረጉት ስምምነት የልጆቻቸውን ጥቅምና ደህንነት በበቂ ሁኔታ የማያስጠብቅ ወይም የአንደኛውን ተጋቢ ጥቅም የሚጐዳ ሆኖ ካገኘው ፍርድ ቤቱ ፍቺውን ብቻ አጽድቆ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ጉድለቶቹ እንዲስተካከሉ ተገቢ መሰሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ሁለተኛው የፍቺ መንገድ

ሁለተኛው ፍቺ የሚደረግበት መንገድ ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም በአንድነት በመሆን የፍቺ ጥያቄያቸውን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍርድ ቤቱ የፍቺውን ውጤት እንዲወስንላቸው ሲጠይቁ  የሚሰጥ የፍቺ አይነት ነው፡፡  በዚህ አይነት የፍቺ መንገድም ፍርድ ቤቱ ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር የፍቺው ጥያቄ የሚተውበትንና አለመግባባቱን በስምምነት ለመፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያግባባቸዋል፡፡ ውጤት ካላገኘ ወይም ውጤት የማይገኝ መሰሎ ከተሰማው ባልና ሚስቱ ራሳቸው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች ከፍርድ ቤት ውጭ ጉዳያቸውን በእርቅ እንዲጨርሱ ሊጠይቃቸው ይችላል፡፡ ይህ ካልተሳካ ከሦስት ወር ያልበለጠ የማስላሰያ ጊዜ በመወሰን ሊያስናብታቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ጥረቶች ተደርገው የአስታራቂ ሽማግሌዎች  ሪፖርት ከደረሰው ወይም ለተጋቢዎች የተሰጠው የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ 

የፍቺ ጥያቄ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ ባልና ሚስቱ ስለሚተዳደሩበትና ስለሚኖሩበት ሁኔታ፣ ስለልጆቻቸው አጠባበቅ ስለሚኖሩበት ስፍራና ሰለአኗኗራቸው እንዲሁም ስለንብረታቸው አስተዳዳር ተገቢ መሰሎ የታየውን ተዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ከሁለቱ ተጋቢዎች የአንዳቸው ከጋራ መኖሪያቸው መውጣት የግድ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ የጋራ መኖሪያቸውን ለቆ ቢወጣ የባሰ ጉዳት የሚደርስበት ወገን የትኛው መሆኑን እንዲሁም የልጆቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ አመቺ የሚሆነውን ሁኔታ ሁሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ 

በፍቺ ጥያቄ መሰረት ጋብቻው የፈረስ እንደሆነ በፍቺው ውጤት ላይ እንዲስማሙ ፍ/ቤት ባልና ሚስቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ የማይሰማሙ ከሆነ ፍርድ ቤቱ በራሱ ወይም በሽማግሌዎች ወይም ፍርድ ቤቱ በሚሾማቸው ባለሙያዎች አማካኝነት ወይም አመቺ መስሎ በሚታየው በማናቸውም ዘዴ የፍቺውን ውጤት ይወስናል፡፡ የፍቺው ውጤት በስምምነት በሚያልቅበት ወይም በሽማግሌዎች ወይም በባለሞያዎች በሚወስንበት ጊዜ ውሳኔው ተፈፃሚነት የሚኖረው ለፍርድ ቤቱ ቀረቦ ተቀባይነት ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍቺውን አስቀድሞ በመወሰን የፍቺውን ውጤት በተመለከተ የሚሰጠውን ውሳኔ እንደሁኔታው ከፍቺ በኋላ ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ሊያዘገየው ይችላል፡፡ የፍቺው ምክንያት የሆነውን በደል ከተጋቢዎቹ አንዱ የፈፀመ እንደሆነ በሌላው ተጋቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በዳዩ ተመጣጣኘ የሆነ ካሳ እንዲከፍል ሊወስን ይችላል፡፡ 

የፍቺ ውጤቶች

ፍቺ ሁለት አይነት የተለመዱ ውጤቶችን የሚያስከትል ሲሆን ውጤቶቹም የሚከተሊት ናቸው፡፡

  1. ፍቺ በንብረት ላይ ያለው ውጤት፣
  2. ፍቺ በተወለዱት ልጆች ላይ ያለው ውጤት ናቸው፡፡

 ፍቺ በንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት

ጋብቻ ከፈረሰ በኋላ በንብረታቸው ላይ ያለውን ውጤት በጋብቻ ውላቸው ላይ ያላስቀመጡ ከሆነ ባልና ሚስቱ የግል ንብረታቸውን መልሰው ይወሰዳሉ፡፡ የጋራ ሀብታቸው ደግሞ ለሁለቱም እኩል የሚከፋፈል ይሆናል፡፡ አስቀድመን ግን በጋብቻ ውስጥ የግልና የጋራ ሀብት ምን እንደሆነ እንይ፡፡ 

የግል ሀብት ምን? – የጋራ ሀብት ?

ተጋቢዎቹ በጋብቻቸው ቀን ወይም ከተጋቡ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ በየግላቸው ያገኙት ንብረት የግል ሀብት ይሆናል፡፡ ከተጋቡ በኋላ አንዱ የግል ሀብቱ በሆነ ንብረት ለውጥ ያገኘው ወይም በግል ገንዘቡ የገዛቸው ወይም የግል ንብረቱን ሸጦ የሚያገኘው ገንዘብ የግል ሀብቱ ይሆናል፡፡ ይህ ተፈፃሚ የሚሆነው በግብይት የተገኘው ንብረት የግል ይባልልኝ ብሎ አንደኛው ወገን ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤት ሲያፀድቀው ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ያሉ ንብረቶች በሙሉ የጋራ ሀብት ይሆናሉ፡፡ ባልና ሚስቱ ከግል ጥረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎችንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ 

ባልና ሚስት የጋብቻ ውል ካላቸው በዚህ ውላቸው ውስጥ የግልና የጋራ ሀብታቸውን መወሰን ይችላሉ፡፡ በፍቺ ጊዜ ወይም ጋብቻቸው በሚፈርስበት ጊዜ ባልና ሚስቱ የግል ሀብቱ መሆኑን በማስረዳት የግል ንብረቱን መልሶ የመውሰድ መብት ይኖረዋል፡፡ ከባልና ሚስቱ አንደኛው የግል ሀብቱ የሆነ ማናቸውም ንብረት ለሌላ ሰው የተላለፈ መሆኑና ከዚሁ ግብይት የተገኘውም  ገንዘብ ከጋራ ሀብታቸው ጋር የተቀላቀለ መሆኑን ያስረዳ እንደሆነ፣ ከዚህ ንብረት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ ወይም ንብረት ከጋራ ሀብታቸው  በቅድሚያ የማንሳት መብት ይኖረዋል፡፡ ባልና ሚስት ከጋራ ሀብታቸው ውሰጥ አስተዋጽኦ ባለበት መጠን ሊደርሳቸው የሚችለውን ያህል የግል ሀብቻቸውን የማንሳት መብት ይኖራቸዋል፡፡

የጋራ ንብረትን ወይም የሌላኛውን ተጋቢ ንብረት በብቸኝነት እንዲያስተዳድር ስልጣን የተሰጠው ተጋቢ የሌላኛውን ተጋቢ ንብረት በብቸኝነት እንዲያስተዳድር ስልጣን  የተሰጠው ተጋቢ ያልሆነውን ተጋቢ መብት ቢጉዳ ፍርድ ቤት በተበዳዩ ጥያቄ ሲቀርብለት ተጋቢ የጉዳት ካሳ እንዲከፈለው ሊያዝ ይችላል፡፡ የአንደኛው ተጋቢ የግል ንብረት ወይም የተጋቢዎች የጋራ ሀብት ከአንደኛው የግል ሀብት ከሆነ ንብረት ያላአግባብ መበልፀጉን ካስረዳ ፍርድ ቤቱ ካሳ እንዲከፍለው ሊያዝ ይችላል፡፡ 

ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም በጋራ በፍርድ የተረጋገጠባቸው ወይም ሁለቱም ያመኑት ዕዳ መኖሩ የታወቀ እንደሆነ የባልና ሚስት ሀብት ከመከፍፈሉ በፊት ተቀንሶ የሚከፈል ይሆናል፡፡ 

የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ለሁለቱም እኩል የሚከፍፈል ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ተጋቢ ከጋራ ሀብቱ የተወሰነ ንብረተ እንዲደርሰው በማድረግ የግራ ሀብቱ በዓይነት እንዲከፍፈል ይደረጋል፡፡ እኩል ለማከፋፈል የማይቻል ሆኖ  ከተገኘ ልዩነቱ በገንዘብ እንዲካስ ይደረጋል፡፡ የሀብት ክፍፍሉ በሚደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ተጋቢ ይበልጥ ጠቃሚነት ያላቸውን ንብርቶች እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት መድረግ ይኖርበታል፡፡ የጋሪ ንብረቱ ለክፍፍል የማያመች ወይም ለማከፍፈል የማይቻል ከሆነና ንብረቱ ለአንዳቸው እንዲስጥ ለማስማማት ካልተቻለ ንብረቱ ተሽጦ ገንዘቡ እንዲከፋፈሉ ይደርጋል፡፡ ስለአሻሻጡ ሁኔታ ሳይሰማሙ ቀርተው እንደኛው ጥያቄ ያቀረበ ከሆነ ሽያጩ በጨረታ ይሆናል፡፡ ጋብቻው ፈርሶ ንብረቱ ከተከፋፊለ በኋላ የሚጠየቅ ዕዳ በጋራ መከፈል የነበረበት ከሆነ ሁለቱም በየድርሻቸው ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ዕዳው አንደኛውን ተጋቢ ብቻ የሚመለከት ከሆነ ባለዕዳ የሆነው ተጋቢ ብቻ ይጠየቃል፡፡ 

የጋብቻ መፍርስ በልጆች ላይ የሚኖረው ውጤት

የጋብቻ መፍረስ ባልጆች ላይም የራሱ የሆነ ውጤት አለው፡፡ የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ በተቻለ መጠን የልጆችንም ጥቅም በሚያስጠብቅ ሁኔታ የጋብቻ   መፍረስ ውጤት መወሰን እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍቺን በሚወስንበተ ጊዜ ልጆች ከማን ጋር ሊኖሩ እንደሚገባ፣ ስለትምህርታቸውና ስለጤናቸው አጠባበቅ፣ ሰለቀለባቸውና ባጠቃላይም ስለአኗኗራቸው እንዲሁም ወላጆችና ልጀች ለመጠየቅ ስላላቸው መብት መወሰን አለበት፡፡ ይህን ውሳኔ ሲያደርግ የወላጆችን የገቢ፣የዕድሜ፣የጤና እና የአኗኗር ሁኔታ እንዲሁም የልጆቹን ዕድሜ፣ጥቅማቸውንና ፍላጐታቸው የሚጠበቅበትን ሁኔታ ማገናዘብ ይኖርበታል፡፡ ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሁኔታዎች ስለወጡና ውሳኔው እንዲሻሻል ጥያቄ ሲቀርብ ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ ይችላል፡፡ የቀለብ ግዴታ በወላጆችና በተወላጆች መካከል እንዳለ በህግ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ወላጆች በጋብቻም ውስጥ ሆነው ወይም ተለያይተው ለልጆቻቸው ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ 

ተጨማሪ ጥያቄ አስተያየት ቢኖርዎት ያነጋግሩን ይጠይቁን

ኢሜይል  ፡-[email protected]

አግባብነትያላቸውተጨማሪህግመረጃዎችከማናቸውምኢትዮጵያዊጠበቃ፣ኢትዮጵያዊየፍቺጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊየቤተሰብጠበቃማግኘትይችላሉ፡፡

Scroll to Top